አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄ፣ ከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ እንዲሁም ሩፋኤል በዓላትን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ እንዳሉት÷ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎቹ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ሳምንት እስከ ጳጉሜን መጨረሻ ይከበራሉ፡፡
በዓላቱ “ባህላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ጠቅሰዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄ፣ የከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ እንዲሁም ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች ሳይበረዙ ተጠብቀው እንዲኖሩና ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ እንዲከበሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቃዊ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በሰሜን ወሎ የተለያዩ ወረዳዎችና በራያ አካባቢዎች እንደሚከበሩ አመልክተዋል፡፡
በዓላቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከበሩ በኋላ ነሐሴ 20 ቀን ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ የበዓላቱ ማጠቃለያ መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በደሳለኝ ቢራራ