የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Shambel Mihret

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በህጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ አማራጭ የባሕር በሮችን ለማግኘት የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ኢትዮጵያ ይህን ህጋዊ እና ሰላማዊ የሆነውን ጥያቄዋ ተከትሎ በተለይም ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር የተፈጠሩ ልዩነቶች እስኪፈቱ ድርስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምትገፋበት አረጋግጠዋል።

ሰሞኑን በሊባኖስ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ተቻኩለው እንዲወጡ የሚያደርግ ነባራዊ ሁኔታ እንደሌለ እና ከሀገሪቱ መንግስትም ቢሆን የውጭ ሀገር መንግስታት ዜጎቻቸውን እንዲያወጡ አለመጠየቁን በማንሳት ዜጎች ተረጋግተው ኑሯቸዉን ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

የተፈጠረው የደህንነት ስጋት ወደ ባሰ ቀውስ የሚሸጋገር ከሆነ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አደጋ እንዳያጋጥማቸው መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ቃል አቀባዩ በሶማሊያ ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) በኋላ የሚደረገው የኃይል ሥምሪት በቀጣናው ላይ አዲስ ውጥረት በመፍጠር በሰላም እና መረጋጋት ላይ አደጋ ሊፈጥር በማይችል መልኩ በጥንቃቄ ሊዋቀር እንደሚገባ ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአትሚስ ሠራዊት አዋጥተው የሚገኙ ሀገራት በጉዳዩ ላይ ወሳኝ ባለድርሻ እንደመሆናቸው በቀጣይ በሚኖሩ የተልዕኮ ሥምሪቶች ላይ አስተያየታቸው ሊጠየቅ ይገባል ተብሎ እንደሚታመን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡

አግባብነት ያላቸው የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔዎችም ይህንኑ እንደሚያስገነዝቡ አምባሳደር ነብዩ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውስጥ ወታደር እንዳዋጣ ሀገር፣ እንደ ጎረቤት እንዲሁም የፀጥታ እና የደኀንነት ድርሻ እንዳላት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችው እንደምትገኝ አብራርተዋል።