አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ዛሬ ሾመ ፡፡
ምክር ቤቱ ሹመቱን ያፀደቀው ዛሬ ባካሄደው 6ኛ የምርጫ ጊዜ 3ኛ የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ ነው።
በምክር ቤቱ የተሾሙት ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ቀደም ሲል በጋምቤላ ክልል የሴቶችና ህፃናት ቢሮ በኃላፊነት እንዲሁም በሌሎች ቢሮዎች በኃላፊነት አገልግለዋል።
ወደዛሬው ሹመት እስከመጡበት ጊዜ ድረስም በኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
የአመራር ለውጥ ያስፈለገበት ምክንያት በክልሉ በሠላምና ፀጥታ እንዲሁም በልማት ዘርፍ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የተቀመጡ አቅጣጫዎች ውስንነቶች በመታየታቸው እና የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ለሌላ የፓርቲ ተልዕኮ በመፈለጋቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲሷ ተሿሚ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ክልሉን ከስድስት አመት በላይ ሲመሩ ከቆዩት ከአቶ ኡሞድ ኡጁሉ የርዕሰ መስተዳድር ስልጣናቸውን በይፋ መረከባቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ምክር ቤቱ የርዕሰ መስተዳድሯን ሹመት በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን÷ ተሿሚዋ በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።
እንዲሁም ጋትሏክ ሮን(ዶ/ር) የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል፡፡
ጋትሏክ ሮን(ዶ/ር) ከዚህ ቀደም የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣በክልሉ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም በጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሆነው እንዳገለገሉ ተገልጿል።
ወደዛሬው ሹመት እስከመጡበት ድረስም የውሃና ኢነርጂ የሚኒስትር አማካሪ ሆነው እያገለገሉ እንደነበር ተጠቅሷል።
ጋትሏክ(ዶ/ር) ክልሉን ከስድስት አመት በላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲያገለግሉ ከነበሩት ከአቶ ቴንኩዌይ ጆክ የምክትልነት ስልጣንን ተረክበዋል።
ምክር ቤቱ የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ሹመት በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን ÷ተሿሚው በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።