የሀገር ውስጥ ዜና

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ተባለ

By Shambel Mihret

August 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎች እንደተፈጠሩ በአለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ዋና ኢኮኖሚስት ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ/ር) ገለጹ።

ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ/ር) የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምርት ሂደትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሀ ይታገሱ (ዶ/ር)፣ በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ/ር)÷ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኙትን ሱፍሌ ማልት ኢትዮጵያ የቢራ ብቅል አምራች እና ሺንትስ የጨርቃጨርቅ አምራች ኩባንያን የምርት ሂደትን ተዟዙረው ተመልክተዋል።

በምልከታቸውም÷ በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተለይም በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪ ዘርፍ ለኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህም ለኢንቨስትመንት ፍሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡