አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ዋጋ በጨመሩ እና ምርትን ባከማቹ 1 ሺህ 435 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ለሸማቾች፣ ለንግድ ማህበረሰብ ጨምሮ 20 ሺህ 942 ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ መፈጠሩንም ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ እና የውጭ ምንዛሪ አስተደደር ሥርዓት ማሻሻያ መመሪያ ትግበራ ክትትልና ቁጥጥር ግብረ-ሀይል ሰብሳቢ ታሪኩ ኩመራ÷ ኮሚቴው እስካሁን በሰራው የክትትል ሥራ በህገወጥ ንግድና ምርት በማከማቸት በተገኙ 1 ሺህ 435 የንግድ ድርጀቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
የክትትል ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ሸማቹ ማህበረሰብ በህገ-ወጥ መንገድ የሚቀሰቀሱ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ መቅረቡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡