የሀገር ውስጥ ዜና

በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ከ72 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው ድጋፍ ተደረገ

By Shambel Mihret

August 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ በቅርቡ በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 72 ሚሊየን 87 ሺህ ብር ዋጋ ያለው ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉም አንድ ተሽከርካሪን ጨምሮ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለጎፋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) ድጋፉን አስረክበዋል፡፡

በአደጋው ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ከ1 ሺህ 300 በላይ ወገኖችን በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት እንዲቻል በሌሎች ቦታዎች ለማስፈር መታቀዱንም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን በአደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

የአደጋው ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚሰራው ሥራ ባለስልጣኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ አረጋግጠዋል።

በመለሰ ታደለ