የሀገር ውስጥ ዜና

ሰዎችን አግተው ገንዘብ ሲቀበሉ ነበር የተባሉ የአሸባሪው ሸኔ አባላት ክስ ተመሰረተባቸው

By ዮሐንስ ደርበው

August 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን እያገቱ ገንዘብ በመቀበል የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ ሦስት የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ክስ ተመሰረተባቸው።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የፌደራል ዐቃቤ ሕግ÷ 1ኛ ከቤ በቀለ ጉታ በቅጽል ስሙ (ጃል ለሊሳ)፣ 2ኛ ለማ ሰሜ መገርሳ በቅጽል ስሙ (ጃል ለሚ) እና 3ኛ አዲሱ አዱኛ ገመዳ በቅጽል ስሙ (ቦሬ) በተባሉ ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 38 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በወንጀል ድርጊትና በሚገኘው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የሸኔ በድን አባል በመሆን፣ የሽብር ቡድኑን የፖለቲካ ዓላማ ተልዕኮ ተቀብለው ሰዎችን በማገት፣ ለሽብር ቡድኑ የሎጂስቲክ ድጋፍ በማስተባበር፣ የመንግሥት ፀጥታ አካላት ላይ ውጊያ በመክፈት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽ ከግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን በማገት፣ ገንዘብ በመቀበል ሚሊሻዎች ላይ ውጊያ በመክፈት ሲንቀሳቀስ እንደነበር፤ 2ኛ ተከሳሽም በ2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሙገር አካባቢ የሽብር ተግባር በመፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ አካባቢ ሰላም በሚያስከብሩ የፀጥታ አካላት ላይ ውጊያ በመክፈት ሰዎችን በማገት ገንዘብ ሲቀበል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በተለያየ ጊዜ ሰዎችን በማገት 309 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በመቀበል፣ 11 መኪኖችን በማቃጠል፣ የ203 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ በማድረግ፣ 362 ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም 52 ጤና ጣቢያዎች፣ 81 ትምህርት ቤቶች፣ 14 የቀበሌ አሥተዳደሮች፣ 1 ሺህ 547 መኖሪያ ቤቶች፣ 3 የሐይማኖት ተቋማት እንዲቃጠሉ በማድረግ፣ 41 ሺህ 145 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ፣ 73 ሚሊየን 88 ሺህ ብር የመንግሥት ገቢ እንዳይሰበሰብ እና አርሶ አደሩ መሬቱን አርሶ እንዳይጠቀም ማድረጋቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል መፈጸም ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹም በተረኛ ችሎት ቀርበው ማንነታቸውን የመለየት ሥራ ከተሠራ በኋላ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ በአስተርጓሚ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላቸው በመግለጽ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡

ተረኛ ችሎቱም ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ በመስጠት በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በማለት ለጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ