አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመዲናዋ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ለተውጣጡ 203 ቤተሰቦች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ዛሬ አከናውኗል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ማግስት አንስቶ አቅም የሌላቸውን ዜጎች ለመደገፍ ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እየተሰባሰበ ይገኛል።
በዛሬው እለትም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ”እናልፈዋለን” በሚል መሪ ሃሳብ ከአራዳ ክፍለ ከተማ አስሩም ወረዳዎች ለተውጣጡ 203 አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የምግብ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም ለእያንዳንዳቸው 50 ኪሎ የስንዴ ዱቄትና 3 ሊትር ዘይት መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ”ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም የሚገጥሙንን ችግሮች በጋራ በመደጋገፍ እና በጽናት በመቆም ስንሻገር ኖረናል” ብለዋል።
ዛሬ ላይ ደግሞ በዓለም ላይ የተከሰተውና እንደ ሃገርም ያጋጠመው ወረርሽኝ እያስከተለ ያለው ችግር በጋራ በመቆም የሚታለፍ እንደሆነ አንስተዋል።
እንደ ሃገር በርካታ ችግሮችን እያለፍን ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፤ ከህዳሴው ግድብ ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች እንደሚያልፉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ በበኩላቸው የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ እያጋጠሙ ያሉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማለፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።