የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገራዊ ምክክር ሥራ ሒደት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተና ተስፋ ሰጪ ነው – የሐረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች

By Melaku Gedif

August 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ የሚገኘው ስራ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በሐረሪ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የሐረሪ ክልል ሰብሳቢ አቶ ተስፋ ሚልኬ÷ በኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታ፣ የህብረተሰብ ተወካዮች መረጣ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብና ሌሎች ተግባራት ሂደቱን ጠብቀው እተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከራስ ፍላጎትና አስተሳሰብ በዘለለ መልኩ “ኢትዮጵያ ምን ያስፈልጋታል? ህዝቡስ ምን ይፈልጋል?” በሚለው ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሐረር ሊቀ መንበር አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድ በበኩላቸው÷ በሀገሪቷ የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ የኮሚሽኑ ስራ አበረታች ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሀገር ልማት፣ እድገትና ሰላም የሚበጁትንና እየተከናወኑ ያሉትን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ የኢዜማ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ት ማህሌት ዘውዱ÷ ምክክሩ ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት እንድንችል የሚያሸጋግር ድልድይ ነው፤ በዚህም ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘው ሥራም ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል የወከሉት አቶ ሀሰን አብዲ በበኩላቸው÷ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ የተሻለ ለማድረግና ሁሉንም የሚያግባባና የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳው የጎላ ነው፤ ስራውም ተስፋ ሰጪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይ በምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈና ሃሳቦች በነጻነት የሚቀርቡበትና በዴሞክራሲያዊ መንገድና ሀገርን የሚያሻግር ውይይት እየተካሄደበት የሚገኝ መድረክ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሀገራዊ ምክክሩ እያከናወነ የሚገኘው ሥራ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ እና ተስፋ ሰጪ እንደሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስገንዝበዋል፡፡