ቢዝነስ

በኦሮሚያ ክልል ከተኪ ምርቶች 800 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

By Melaku Gedif

August 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ከተኪ ምርቶች 800 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አሕመድ እድሪስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በክልሉ ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀሩ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡

የመስሪያ ቦታ እና የብድር አገልግሎት በተኪ ምርቶች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ በዚህም ተኪ ምርቶችን ለማምረት የሚሰማሩ አልሚዎቸ ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ነው ያስረዱት፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 800 ሚሊየን ዶላር ገቢ ምርትን በክልል በማምረት የውጭ ምንዛሬን ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም እንደ ሀገር የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በተኪ ምርቶች ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው÷ አልሚዎች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ