ጤና

የሳምባ ካንሰር መንስዔ፣ ምልክቶችና ህክምናው

By ዮሐንስ ደርበው

August 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳምባ ካንሰር በተለምዶ የሳምባ ነቀርሳ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በሳምባ ውስጥ ጤነኛ ያልሆኑ ህዋሳት ቁጥር ሲበዙ የሚከሰት ነው፡፡

የእነዚህ ህዋሳት ከቁጥጥር ውጪ መብዛት የሳምባን የተለመደ አሰራር በማወክ ችግሩ ወደ ሌላ የሰውነት አካላት እንዲሰራጭ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

የሳምባ ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች ምንድናቸው?

ሲጋራ ማጨስ ለሳንባ ካንሰር ዋነኛ አጋላጭ ምክንያት ሲሆን÷በሚያጨሱ ሰዎች አካባቢ የሚገኙ ደባል አጫሾችም ለሳንባ ካንሰር የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

እንደ አስቤስቶስ፣ ሲሊካ፣ ራዶን፣ ከባድ ብረቶች፣ፖሊሳይክሊክ እና ሃይድሮካርቦን የመሳሰሉ ኬሚካሎች ያሉባቸው የስራ ቦታዎችም ለሳምባ ካንሰር አጋላጭ ናቸው፡፡

እንዲሁም በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ የሚኖር የአየር ብክለት ለሳምባ ካንሰር ተጋላጭ ያደርጋል፡፡

የሳምባ ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ በዘር የመተላለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ መሆኑንም የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም  በተደጋጋሚ በደረት ላይ የሚደረግ የጨረር ምርመራ በሳምባ ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ከፍ ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩትን አጋላጭ ሁኔታዎች መቀነስ ወይም ማስወገድ የሳምባ ካንሰርን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

የሳምባ ካንሰር ዋና ዋና ምልክቶች ምንድናቸው?

ለረጅም ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ወይም በቀላሉ የማይጠፋ ሳል፣ የደረት ህመም፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ስንተነፍስ ድምጽ መኖር፣ ደም የቀላቀለ አክታ፣ በብዛት የሚሰማ የድካም ስሜት፣ ባልታወቀ ምክንያት ክብደት መቀነስ፣ በተደጋጋሚ ለሳምባ ምች መጋለጥ የሳምባ ካንሰር ምልክቶች ናቸው ፡፡

በመሆኑም እነዚህን ምልክቶች ከተመለከቱ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ይገባል፡፡

የሳምባ ካንሰር ሕክምና:-

የሳምባ ካንሰር እንደ አይነቱ እንዲሁም እንደሚገኝበት የስርጭት ደረጃ በብዙ መንገዶች የሚታከምና በጊዜ ከተደረሰበት ሊድን የሚችል ህመም ነው፡፡

በዚህም በቀዶ ሕክምና፣ በኬሞቴራፒ፣ በጨረር ሕክምና እና በሌሎች ህክምናዎች መታከም የሚችል መሆኑን የሄልዝ ላይን መረጃ ያሳያል፡፡