አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በብሔራዊ ቤተ መንግስት የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የስፖርቱ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡
በእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብሩ በወንዶች ማራቶን ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ 7 ሚሊየን ብር እና የወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።
እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ የብር ሜዳልያ ላመጡት አትሌት ትግስት አሰፋ፣ በሪሁን አረጋዊ እና ፅጌ ዱጉማ ለእያንዳንዳቸው የ 4 ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡
በ3ሺህ ሜትር መሰናክል ሀገሩን የወከለውና ውድድሩን ተደናቅፎ በመውደቁ ምክንያት ሳያጠናቅቅ ለቀረው አትሌት ለሜቻ ግርማ የ2 ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
በወንዶች ማራቶን ለሀገሩ ለተወዳደረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ የወርቅ ኒሻን ተበርክቶለታል፡፡
በፓሪስ የኦሊምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ÷በኦሊምፒኩ 1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎች በማግኘት 47 ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወቃል።