አዲስ አበባ፣ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በየክልል ከተሞች ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ 1 ሺህ 671 የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውን አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከብሄራዊ የንግድ ተቋማት የፀረ ህገ ወጥ ንግድና ገበያ መቆጣጠርያ የጋራ ኮሚቴ ጋር ግምገማ አካሂደዋል፡፡
በዚህ ወቅት በየክልል ከተሞች ህገ ወጥ የንግድ ተግባራትን የፈፀሙ 1 ሺህ 671 የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውንና ከዚህ ቀደም በሰሩት ህገ ወጥ የንግድ ተግባራት ምክንያት ታሽገው የነበሩ 18 ሺህ 789 ድርጅቶች ደግሞ የውል ስምምነት ፈፅመው ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከህገ ወጥ ንግድ ጋር በተያዘ ዛሬ የታሰሩትን 82 ነጋዴዎች ጨምሮ እስካሁን በድምሩ 628 ነጋዴዎች የታሰሩ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 182 ነጋዴዎች ከእስራት የተፈቱ መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥርም በዛሬው እለት ብቻ በግንባታ እቃዎች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 21 የሲሚንቶ፣ 7 የብረት፣ 10 የቆርቆሮ፣ 3 የሚስማር እና 2 የሴራሚክ የንግድ ተቋማት ታሽገዋል፡፡
በየጊዜው በተደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ በዱቄት፣ ስኳር፣ ቲማቲም፣ ድንችና በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ መታየቱን ገልጸዋል፡፡
ገበያ የማረጋጋት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ ቀናት በጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ መጠቆማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡