Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የሰለጠኑ ሴቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በነገዋ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሴቶች ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ እና የተሰጣቸውን ስልጠና በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ ሴቶችን አስመርቀናል ብለዋል።

ሰልጣኞቹ በ5 የስልጠና ክፍሎች እና በ18 የሙያ ዘርፎች ለአራት ወራት ስልጠና እና የስነ ልቦና ምክር በማግኘት ከነበሩበት አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለመውጣት ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በቀጣይ በስራ ሂደት ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመው÷ ሰልጣኞቹ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው የመስሪያ ቦታ ቁልፎችን በዛሬው ዕለት መረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን በሚያከናውንበት ወቅት ከመንግስት ጎን ለቆሙ ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የነገዋ የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ውጤታማ በመሆን ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም በርካታ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት የደረሰባቸውን ሴቶችን ህይወት መጠገን እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version