Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የስራ እድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ስራ እድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በበጀት አመቱ 20 በመቶ ላይ የሚገኘውን የክልሉን የስራ አጥነት ምጣኔ ወደ 19 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ያቀደው ቢሮው፤ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለባለድርሻ አካላት አስተዋውቋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመሠረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በቀጣዮቹ አምስት አመታት የክልሉ መንግስት ስራ ዕድል ፈጠራን የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ መያዙን ተናግረዋል።

በስራና ስልጠና ቢሮ በኩል በ2017 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙንም ነው የገለጹት፡፡

ለዚህ እቅድ መሣካት የሚሆኑ 3 ሺህ 500 ማምረቻ ሼዶች እንደሚገነቡ ጠቁመው፤ በህገወጥ መንገድ የተያዙ 5 ሺህ ሼዶችና ኮንቴነሮች እንዲመለሱ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከ5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር ለኢንተርፕራይዞች እንደሚፈጠር ቢሮው በእቅዱ አሳይቷል።

በእሌኒ ተሰማ

Exit mobile version