አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለ አግባብ ዋጋ የጨመሩ ከ3 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ ÷በክልሉ በምርቶች ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ የንግድ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በተደረገ ክትትልም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 3 ሺህ 353 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውንና 57 ነጋዴዎች መታሰራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ምርቶች ላይ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 7 ሺህ 167 የንግድ ድርጅቶች ላይም የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠ አንስተዋል፡፡
ከድርጊታቸው መቆጠብና መታረም ያልቻሉ 71 ድርጅቶች ደግሞ በገንዘብ መቀጣታቸውን ገልጸው ሸማቹ ህብረተሰብ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማስተዋል አሰፋ