ጤና

የኮማንዶና የአየር ወለድ ዕዝ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ሀይሎችን አስመረቀ

By Amele Demsew

August 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮማንዶና የአየር ወለድ ዕዝ ስር የሚገኘው የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ‘አዳኞቹ’ በሚል መጠሪያ ያሰለጠናቸውን 12ኛ ዙር የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ሀይሎችን አስመረቀ።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።

ተመራቂዎቹ ከዕዙ የተለያዩ ክፍሎች በግዳጅ አፈፃፀማቸውና በዲሲፕሊናቸው የተመረጡና የተሰጠውን አስቸጋሪ ስልጠና በአጥጋቢ ሁኔታ ያጠናቀቁ መሆናቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመልክቷል።

ተመራቂዎቹ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚሰጣቸውን ግዳጅ በተናጠልም ሆነ በቡድን ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስልጠና የወሰዱ መሆናቸው ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ በተመራቂዎቹ የተለያዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች የቀረቡ ሲሆን፤ በክብር እንግዳው የተመራው የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችም በዕዙ የልዩ ሀይልና የፀረ ሽብር ማሰልጠኛ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።