ስፓርት

ከኢትዮጵያ ርቆ የቆየውን የማራቶን ኦሊምፒክ ድል በማስመለሴ ደስ ብሎኛል – አትሌት ታምራት ቶላ

By Mikias Ayele

August 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ ርቆ የቆየውን የማራቶን ኦሊምፒክ ድል በማስመለሴ ደስ ብሎኛል ሲል በኦሊፒኩ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ታምራት ቶላ ተናገረ፡፡

አትሌት ታምራት ቶላን ጨምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

አትሌት ታምራት በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማሪፊያ በነበረው የአቀባበል ስነ ስርዓት ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ በማራቶን የምትታወቅ ሀገር መሆኗን አስታውሷል፡፡

ይሁን እንጂ የማራቶን ድል ከኢትዮጵያ ርቆ መቆቱን ጠቅሶ፤ በፓሪሱ ማራቶን ኢትዮጵያን ወደ ምትታወቅበት የማራቶን ድሏ መመለስ በመቻሉ መደሰቱን ተናግሯል፡፡

በውድድሩ የፓሪስ አየር ፀባይ ሞቃታማ መሆኑ እንዲሁም በማራቶን ልምድ ያላቸው አትሌቶች መሳተፋቸው ውድድሩን ከባድ አድርጎት እንደነበር ጠቅሷል፡፡

ይሁን እንጂ ሁሉንም ተቋቁሞ ለድል መብቃቱን የገለፀው አትሌቱ÷ ድጋፉን ለገለፀለት የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አሰልጣኞችና የቡድን አመራሮች ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ተጠባባቂ ከነበረበት የፓሪሱ ኦሊምፒክ የማራቶን የውድድር ተሳትፎ እንዲያገኝ እድል ለሰጠው እና የማራቶን ቡድን አጋሩ ለሆነው ሲሳይ ለማ ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ታሪክ በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው ከ24 ዓመታት በፊት በአውስትራሊያ ሲድኒ በተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በአትሌት ገዛኸኝ አበራ አማካኝነት መሆኑ ይታወሳል።

 

በሚኪያስ አየለ