አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ያለ አግባብ ዋጋ የጨመሩ 5 ሺህ 12 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በክልሉ በምርቶች ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ የንግድ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡
እስካሁን በተደረገ ክትትልም ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 5 ሺህ 12 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን፣ 93 ነጋዴዎች መታሰራቸውንና የአንድ ንግድ ተቋም ፈቃድ መሰረዙን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ምርቶችን ሲሰውሩና ሲያከማቹ የተገኙ 541 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን ጠቁመው÷ 42 የሚሆኑት ደግሞ በእስር መቀጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋጋ በመጨመርና ምርት በመሰውር ተግባር ታሽገው የነበሩ የንግድ ተቋማት አብዛኛዎቹ ጥፋታቸውን አምነው ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በንግድ ተቋማት ቁጥጥር መደረጉን ተከትሎም በምርቶች ላይ ተስተውሎ የነበረው የዋጋ ጭማሪ ወደ ነበረበት እየተመለሰ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው÷ ሸማቹ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲያገኝ ለሚመለከተው አካል እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ