የሀገር ውስጥ ዜና

በዛሬው ዕለት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 1 ሺህ 126 የንግድ ተቋማት ታሸጉ

By Melaku Gedif

August 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 1 ሺህ 126 የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ሕገ-ወጥ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪና ምርትን የማከማቸት ተግባራት ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በዚህ መሰረትም በዛሬው ዕለት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 1 ሺህ 126 ተቋማት መታሸጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ ባለፈም የአራት ተቋማት ንግድ ፍቃድ የታገደ ሲሆን÷ የሁለት ተቋማት የንግድ ፍቃድ መሰረዙንም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ 53 ምርት የደበቁ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን ጠቁመው÷ ከዚህ ጋር ተያይዞ የ22 ተቋማት ንግድ ፍቃድ ታግዷል ብለዋል፡፡

እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር የሕግ ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው ታሸገው ከነበሩት መካከል 28 ሺህ 634 የንግድ ተቋማት በሕግ አግባብ ብቻ ለመስራት ዝግጁ በመሆናቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የእስራት እርምጃ ከተወሰደባቸው 5 ሺህ 94 ነጋዴዎች ውስጥ 164 ነጋዴዎች ከእስራት መፈታታቸውን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የግንባታ እቃዎች ላይ እየተደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥር ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 37 የሲሚንቶ፣13 የብረት፣21 የቆርቆሮ እና 5 የሴራሚክ ንግድ ተቋማት መታሸጋቸውንም አንስተዋል፡፡