አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሆላንድ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአፈር ማዳበሪያ ምርት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን ሙሐመድ ከሆላንድና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ባለሃብቶች ጋር በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ባለሃብቶቹ በዚህ ወቅት÷ተፈጥሯዊ የማዳበሪያ ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት ለመንግስት እና ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሃሰን በበኩላቸው ÷ባለሃብቶቹ በማዳበሪያ ምርት ዘርፍ ከተሰማሩ የስራ እድልን በመፍጠር እና የውጪ ምንዛሬ ወጪን በማዳን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም አሲዳማ አፈርን ማከም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ይህ አይነቱ ኢንቨስትመንት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷በተለይም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡