አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃን በተገቢው ሁኔታ ለመጠበቅና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ችግኞችን በየጊዜው መትከል ይገባል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በጋምቤላ ክልል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርና ለተማሪዎች የትምህር ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃን በተገቢው መንገድ ለመጠበቅ የደን ሀብቶችን ማሳደግና ችግኞችን መተከል ይገባል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ችግኝ መትከልና መንከባከብን ለትውልድ በማሻገር ከብክለት የፀዳች ሀገርን ማስረከብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማቱ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ላፕቶፕ ያበረከቱላቸው ሲሆን÷ የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
በተጨማሪም የወንዞች ሙላትና የጎርፍ አደጋ ሲከሰት መጓጓዝ የሚያስችል የሞተር ጀልባ ለክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስረክበዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን