አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 122 ነጋዴዎች በሰሩት ስህተት ተፀፅተው ለመታረም ዝግጁ በመሆናቸው ይቅርታ እንደተደረገላቸው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ÷ ህገ ወጥ የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ እና የማከማቸት ተግባር ላይ እየተደረገ ያለው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት ብቻ ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ 217 ተቋማት መታሸጋቸውን፣ የአንድ ተቋም የንግድ ፍቃድ መሰረዙን እንዲሁም ምርት የደበቁ ስምንት የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ ሶስት ተቋማት ደግሞ ፍቃዳቸው መሰረዙን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የህግ ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው ታሸገው ከነበሩ የንግድ ተቋማት መካከል 27 ሺህ 78 የሚሆኑት ተከፍተው ወደ ስራ የተመለሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እስካሁን የእስራት እርምጃ ከተወሰደባቸው 430 ነጋዴዎች ውስጥ 122 ነጋዴዎች በሰሩት ስህተት ተፀፅተው ለመታረም ዝግጁ በመሆናቸው ከእስራት መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተደረጉ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ ቲማቲም፣ ድንችና በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የዋጋ መረጋጋት መታየቱን የገለጸው የሚኒስቴሩ መረጃ፤ ዋጋ የማረጋጋት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።