Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

31 ክብረ ወሰኖች የተሻሻሉበት የፓሪሱ ኦሊምፒክ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንሳይ አስተናጋጅነት የተካሄደው 33ኛው የፓሪሱ ኦሊምፒክ 31 አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ሲመዘገቡበት በርካታ አይረሴ ድራማዊ ክስተቶችንም አስተናግዶ አልፏል፡፡

የደቡብ ኮሪያ አትሌቶች በመድረኩ የሰሜን ኮሪያ ተብለው መጠራታቸው እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ብሄራዊ መዝሙር ምትክ የሱዳን ብሄራዊ መዝሙር መለቀቁ ኦሎምፒኩን አነጋጋሪ አድርገውት ቆይተዋል፡፡

በበርካታ ውድድሮች ከሁለት ሳምንት በላይ በፓሪስ ሲካሄድ በቆየው የኦሊምፒኩ ጨዋታዎች አሜሪካ በ126 ሜዳሊያዎች ለ7ኛ ጊዜ ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ ቻይና በ91 እንዲሁም ጃፓን በ45 ሜዳሊያዎች ተከታዩን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በውድድሩ በአጠቃላይ 31 አዳዲስ ክብረ ወሰኖች የተመዘገቡ ሲሆን ይህም 22 ክብረወሰኖች ከተመዘገቡበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋር ሲነፃፀር የዘጠኝ ብልጫ አለው፡፡

አትሌቲክስ፣ ተራራ መውጣት፣ የውሃ ቀዘፋ፣ የብስክሌት ውድድር፣ ሞደርን ፔንታሎን (ኢላማ)፣ ውሃ ዋና እና ክብደት ማንሳት በኦሊምፒኩ ክብረ ወሰን የተመዘገበባቸው የስፖርት ዘርፎች ናቸው፡፡

አሜሪካዊቷ ሲድኒ ማክላፊን 4 በ400 የዱላ ቅብብል፣ ስዊድናዊው አርማንድ ዱፕላንት በምርኩዝ ዝላይ፣ ፈረንሳዊው ዋናተኛ ሊዮን ማርቻንድ ክብረ ወሰን ያስመዘገቡ ወጣት አትሌቶች ናቸው፡፡

በተጨማሪም አርሻድ ናዲም ከፓኪስታን በጦር ውርወራ፣ ሮክ ስቶና ከጃማይካ በዲስክ ውርወራ፣ በሴቶች 400 ሜትር ማሪየልዲ ፖሊኖ ከዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ በወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ኮል ሆከር ከአሜሪካ፣ በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ዊንፈሬድ ያቪ ከባህሬን የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን በማሻሻል ስማቸውን በመዝገብ ላይ አስፍረዋል።

በማራቶን በሁለቱም ጾታ የኦሊምፒኩ ክብረ ወሰን የተሻሻለ ሲሆን በወንዶች ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ታምራት ቶላ 2:06:26 በሆነ ሰዓት በመግባት ክብረ ወሰኑን አሻሽሏል።

በሴቶች ደግሞ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን 2:22:55 በመግባት የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን ያሻሻለች ሲሆን፤ ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሽዋ ቴፕቴጌይ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር የኦሊምፒኩን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችለዋል።

Exit mobile version