አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋሞ ብሔረሰብ አባላት ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ስርዓት የሚከናወንበት እና ሰላም የሚወርድበት ስፍራ “ዱቡሻ” በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን የጋሞ ዞን አስታወቀ።
“ዱቡሻ” ሰዎች ወደ ጥፋት መንገድ እንዳይሄዱ፣ በስርዓት፣ ወግና ባህል ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያስችል ባህላዊ የእርቅ ሥነ-ስርዓት የሚከናወንበት አደባባይ መሆኑን የዞኑ መረጃ አመልክቷል።
የጋሞ አባቶች በእጃቸው እርጥብ ሳር ከያዙ ቁጣ ይበርዳል፣ ለፀብ ወይም ለበቀል የተነሳ ማንኛውም አካል ከዱላ ጀምሮ ጥቃት ለመሰንዘር የያዘውን ቁሳቁስ መሬት ያስቀምጥና ጉዳዩ በ”ዱቡሻ” ስርዓት እንዲታይ ይደረጋል፡፡
የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ÷ ዱቡሻ እንደ አዳራሽ የሚታይ የእርቅ ጉዳዮች ሲኖሩ ውሳኔ የሚሰጥበትና የሚመከርበት አደባባይ መሆኑን ገልጸዋል።
ስርዓቱ በሚከናወንበት ስፍራ ውሸት የለም ያሉት ሃላፊው÷ በየአካባቢው ያሉ ዱቡሻዎች የየራሳቸው ደረጃዎች እንዳሏቸው ጠቅሰዋል።
ዱቡሻ በቅርስነት እንዲጠበቅ ዞኑ ከደቡብ ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመሆን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሀገር በቀል እውቀት ጥናትና ልማት ባለሙያ አቶ ዳዊት ሻታ÷ ዱቡሻ ማህበራዊ፣ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የእርቅ ጉዳዮች የሚከወኑበት ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለስፍራው የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ክብር እንዳላቸው ገልጸው፤ ቦታው እርቅ የሚፈጸምበት፣ መረጃ ያጡ ጉዳዮችና ከበድ ያሉ ግጭቶችም እልባትና ፍትህ የሚያገኙበት ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በዞኑ የወሰን ግጭቶች፣ ከአጎራባች ዞኖች ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ የዱቡሻ ሥርዓት ሲከወን የራሱ መገለጫ የሆነ የአለባበስ ሁኔታ እንዳለው ተናግረዋል።
ስርዓቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የዱቡሻ ስፍራዎችን የመጠገን እና በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ስርዓቱን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዱቡሻ ስፍራ መዋሸት ቅጣቱ እርግማን እንዲሁም ከማኅበረሰቡና ከማኅበራዊ አገልግሎቶች መገለል በመሆኑ በዳይም ተበዳይም ለእውነት ተገዢ እንደሚሆኑ የጋሞ ዞን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የወንጀልና የፍትሐብሔር የክሥ መዝገቦች በዱቡሻ እልባት እንደሚያገኙ በመጥቀስ፤ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ በመሆኑ ስርዓቶች እንዲዳብሩ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በየሻምበል ምሕረት