ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያና ዩክሬን በኒውክሌር ጣቢያ ላይ በተነሳው የእሳት አደጋ ተወነጃጀሉ

By Meseret Awoke

August 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን እና ሩሲያ በግዙፉ ዛፖሪዝዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ምክንያት እርስ በርስ መወነጃጀላቸው ተሰምቷል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እንደተናገሩት፥ በሩሲያ ከሁለት ዓመት በላይ ሲተዳደር የነበረው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እሳት እንዲነሳ ምክንያቷ ራሷ ሞስኮ ናት ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

በአንጻሩ ሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያው በእሳት እንዲያያዝ ያደረግሽው አንች ነሽ ስትል ዩክሬንን መልሳ ወንጅላለች ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ቡድን፥ ከጣቢያው ከፍተኛ ጥቁር ጭስ ሲወጣ ማየቱን ገልጾ፥ ሆኖም ግን በኒውክሌር ደህንነት ላይ የደረሰ አሳሳቢ ነገር የለም ሲል ጠቁሟል፡፡

ዩክሬን ወደሩሲያ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መግባታቸው ሲገለጽ የቆየ ሲሆን ይህንንም የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ማረጋገጣቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ነው ግዙፉ የኒውክሌር ጣቢያ በእሳት መያያዙ ነው የተገለጸው፡፡

ሆኖም የሩሲያ አንድ ባለስልጣንና ዘለንስኪ በኒውክሌር ጣቢያው እሳት ቢነሳም የጨረር ልቀትና የኒውክሌር አደጋ እንዳልተፈጠረ በማረጋገጥ መረጋጋት እንዲኖር ጠይቀዋል ነው የተባለው፡፡

አሁን ላይ እሳቱ እንደጠፋ የተገለጸ ቢሆንም፥ የኒውክሌር ጣቢያው ላይ የተከሰተው እሳት ከዚህ ቢብስ ለመላው የአውሮፓ ሀገራት የሚተርፍ ትልቅ አደጋ ሊያስከትል ይችል እንደነበር ተገልጿል።