አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የጨመሩና ምርት ደብቀዋል የተባሉ ከ990 የሚልቁ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ መወሰዱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ዳንኤል ዳምጠው ተናግረዋል፡፡
የሸቀጦች ዋጋ በመጨመርና ምርቶችን በመደበቅ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ለመከላከልም ግብረ-ኃይል ተደራጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ዋጋ በጨመሩና ምርት አከማችተው በተገኙ ከ990 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ የቃል፣ የጽሑፍና የማሸግ ርምጃ መወሰዱን ገልጸው÷ ከ700 ሺህ ብር በላይ መቀጣታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ የግብርና፣ የኢንዱስትሪም ሆነ የሌሎች ምርቶች እጥረት አለመኖሩን አረጋግጠው÷ በግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡