Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ የጨመሩ 3 ሺህ 512 የንግድ ተቋማት ታሸጉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራት ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከብሔራዊ የንግድ ተቋማት የጸረ- ሕገ ወጥ ንግድና ገበያ መቆጣጠሪያ የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር በሕገ ወጥ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪና ምርትን የማከማቸት ሕገ-ወጥ ተግባራት ዙሪያ በክልሎች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገምግመዋል።

12ኛ ቀኑን ባስቆጠረው በዚሁ ግምገማ በትናንትናው ዕለት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 3 ሺህ 512 ንግድ ተቋማት እንደታሸጉና 38 ነጋዴዎች ደግሞ በእስራት መቀጣታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ምርትን አላግባብ የደበቁና ያከማቹ 2 ሺህ 95 የንግድ ተቋማት የታሸጉ ሲሆን÷ወጣ ያለ የህግ ጥሰት ያሳዩና ለህግ ተገዢ ለመሆን ፈቃደኛ ባልሆኑ 212 ነጋዴዎች ላይ ደግሞ የእስራት ቅጣት መተላለፉን አስታውቀዋል።

እስከትናንት ድረስ በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል የሕግ ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው ከታሸጉት የንግድ ተቋማት መካከል ዛሬ 24 ሺህ 386 ተቋማት በሕግ አግባብ ለመስራት በመስማማታቸው ተከፍተው ወደ ሥራ የገቡ መሆኑን አንስተዋል።

በግንባታ እቃዎች ላይ ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 59 የሲሚንቶ፣ ዘጠኝ የብረት እና 10 የቆርቆሮ ንግድ ተቋማት መታሸጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ለሕግ ተገዢ ለመሆን ፍቃደኛ ያልሆነ አንድ የሲሚንቶ ነጋዴ በእስር መቀጣቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በየደረጃው ባለው የመንግስት መዋቅርና ህብረተሰቡ በቅንጅት እየተደረገ ባለው የቁጥጥርና ክትትል ስራ በአብዛኛው ከተሞች በፍጆታ ዕቃዎች በተለይም በምግብ ዘይት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ እየታየ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡

Exit mobile version