አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሎች በህብረት ስራ አማካኝነት ሰፊ የቤት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል ስራ እየተሠራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ የ2016ዓ.ም በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2017 በጀት አመት ዕቅድ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በመደረኩ እንደገለፁት÷ የከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ የተሰሩ የልማት ስራዎች አመርቂ ናቸው፡፡
በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም አሁንም የቤት እጥረቱን ለመቅረፍ በስፋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመሆኑም የህብረት ስራ ማህበራትን በማሳተፍ የቤት አቅርቦትን ለማስፋፋት የሚያስችል ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለፁት ሚኒስትሯ÷ በቀጣይ በከተሞች የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ለመተግበር እና የላቀ አፈፃፀም ለማምጣት በጋራ መግባባት እና በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በቤዛዊት ከበደ