የሀገር ውስጥ ዜና

ዳሽን ባንክና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለጎፋ ዞን አደጋ ተጎጂዎች የ15 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ

By Shambel Mihret

August 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳሽን ባንክ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ15 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የዳሽን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጥበብ ሰለሞን ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት÷ ዞኑ ተጎጂዎችን ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ሂደቱን ለመደገፍ የ10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይለብርሃን ዜና÷ ኮርፖሬሽኑ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ተግባር የ5 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ተጎጂዎችና ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በኢብራሂም ባዲ