Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኦሮሚያ ክልል ለ3 ሺህ 747 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 147 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 3 ሺህ 747 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ያለመ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አሕመድ እድሪስ፣ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የቢሮው ሃላፊ አሕመድ እድሪስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥በኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ለዚህም ምቹና ቀልጣፋ አሰራር ከመዘርጋት ባለፈ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ቁጥር መጨመሩን አንስተዋል።

ከ147 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 3 ሺህ 747 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በክልሉ በዘርፉ 579 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የገለፁት ሃላፊው በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በማምረት ረገድም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ አልሚዎች ከመሬት ጀምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ የሃይል እጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

ባለሃብቶች በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት ግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version