Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሠራዊቱ ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያበረክታል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሠራዊት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያበረክት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ከመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በመንግስት ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ሀገራችን ሁሉ ዓቀፍ ተሰሚነትና ዲፕሎማሲ ትልቅ ድል ያመጣ ስለሆነ ለተግባራዊነቱ ሰራዊቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ያበረክታል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሰራዊቱ እንደሀገር ሰላምና ፀጥታን ከማስከበር ጀምሮ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል በማለት ገልጸው፤ እንደ ተቋም ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ በሙሉ አቅም እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ማሻሻያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አካል ሆኖ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ እንደ ውስጣዊ አቅምን በማጎልበት ቀጠናዊ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናችን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የሀገር እድገት እና የህዝብ ጥቅም የሚረጋገጠው ሰላም ሲሰፍን፣ ህግና ስርዓት ሲከበር ነው ያሉት የገንዘብ ሚንስትሩ÷ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመተግበር የጋራ ኃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መከላከያ እንደተቋም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሙሉ አቅም መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሚያበረታታ ጅማሮ ላይ መሆኑን በማሳያዎች አመላክተዋል፡፡

በቀጣይም የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲን በማስተካከልና በገበያ የሚመራ አስተዳደር በመዘርጋት የብሄራዊ ባንክን የመቆጣጠርና የማስፈፀም አቅምን በማጎልበት እንደሚሰራ መግለፃቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version