Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ በቅድሚያ በቅርቡ ከተደረገው ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ እየታየ ያለን ምንም የገበያ መሰረት የሌለው ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ላይ ተወያይቷል፡፡

በዚህም በተለይ የተለያዩ መሠረታዊ ሸቀጦችን በመሸሸግና የገበያ ዕጥረት ያለ በማስመሰል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የማድረግና ኅብረተሰቡን ለብዝበዛ የመዳረግ ሁኔታዎች በመታየት ላይ መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

ለዚህም በህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራት የንግድና የገበያ ስርዓቱን በሚያዛቡ አካላት ላይ ጠንካራ ክትትል በማድረግ የማስተካከያ ህጋዊ እርምጃዎች በመወሰድ ኅብረተሰቡን ካልተገባ ብዝበዛ ለመታደግ አቅጣጫ አስቀመጧል፡፡

በመቀጠልም ከክረምቱ የዝናብ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና የአደጋ ስጋት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በመነጋገር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ በክልሉ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል ስራ ሲሰራ ቢቆይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በመጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ የመጣል ሁኔታ መኖሩና ከዚህ ጋር ተያይዞ የናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ በተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመደገፍ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ መክሯል፡፡

በተጨማሪ ምክር ቤቱ የአደጋ ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ የተጀመረው አደጋን አስቀድሞ የመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት ኅብረተሰቡን በማንቃትና በንቃት በማሳተፍ ማጠናከር የሚቻልበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የክልሉን አደጋ ስጋት ስራ አመራር አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት አቅም ማጎልበት እንደሚገባም በውይይቱ መነሳቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድድር ጽ/ቤጽ መረጃ አመልክቷል፡፡

በተያያዘም በክልሉ የተጀመሩ የተራራ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችን ጨምሮ የተፈጥሮ ጥበቃና እንክብካቤ ስራውን ማጠናከር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቁልፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ አዋጅ፣ የሰንደቅ አላማ አዋጅ፣ የፖሊስ አባላት መተዳደሪያ ደንብ እና የታራሚዎች ደንብ ላይም ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

መስተዳድር ም/ቤቱ የክልል ማዕከላትና ሴክተር ቢሮዎች የበጀት ድልድል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በመወሰንና ቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቅቋል፡፡

Exit mobile version