አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የሀዲያ አዲስ ዓመት የያሆዴ በዓልን በጋር ለማክበር የሚያስችል የጋራ የውል ስምምነት በሀዲያ ዞን እና ሻኩራ ፕሮዳክሽን መካከል ተፈረመ።
የሀዲያ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ እንደገለጹት፤ መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴቶቻቸውንና ባህላዊ ክዋኔያቸውን ማሳደግና ማበልጸግ ይገባል።
የያሆዴ በዓልን ከብሔር ተወላጆች ባለፈ ለመላው አለም በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ ሻኩራ ፕሮዳክሽን ካሉ ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራት ውጤት እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።
የሻኩራ ፕሮዳክሽን መስራቹ የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሣ፤ የሀዲያ ህዝብ የዘመን መለወጫ ያሆዴ በዓልን በደማቁ ለማክበር ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በጋራ ለመስራት የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥ ተገልጿል።