የሀገር ውስጥ ዜና

አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የ536 ሚሊየን ዶላር ሰብዓዊ ድጋፍ አደረገች

By Mikias Ayele

August 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከሰሃራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የ536 ሚሊየን ዶላር ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች፡፡

የሀገሪቱ ሲቪል ደህንነት፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ዋና ጸሃፊ ኡዝራ ዘያ÷በኬንያና በኢትዮጵያ ጥሩ ቆይታ እንደነበራቸውና ዘርፈ ብዙ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ፣ ከፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

የአሜሪካ መንግስት እና የሲቪል ማህበረሰብ አጋሮች ከኢትዮጵያ ጋር በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ  በትብብር እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

ዋና ጸሐፊዋ ከኢትዮጵያና ኬንያ በተጨማሪ÷ ኮትዲቯር፣ ጊኒ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያ እና ጋምቢያን ጨምሮ በአፍሪካ  በተለያዩ ሀገራት ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሀገራቱ ባደረጉት ጉብኝትም የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች፣ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እና የሌሎችን ሕይወት የተሻለ ለማድረግ የጋራ መፍትሄዎችን ለመፍጠር የሚሰሩ ጠንካራ  ግለሰቦችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከ38 ሚሊየን በላይ በተለያየ ሁኔታ ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 30 ሚሊየኑ በሀገራቸው ውስጥ የሚገኙ ሲሆን÷ 8 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ድንበር ያቋረጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች እንደምትገኝም አውስተዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስትም ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል አዲስ የ536 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይፋ እንዳደረገ መግለጻቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡