አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክኅሎት ልማት ላይ የሚሠራው ዓለም አቀፉ”ወርልድ ስኪል” ተቋም ኢትዮጵያን 88ኛ አባል አድርጎ መመዝገቡ ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ተቋም አባል መሆኗ ለወጣቶች ክኅሎት፣ ሙያቸውም ቦታ እንዲኖረው የሚያግዝ ትልቅ ዕድል መሆኑን የሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚል ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በመጪው መስከረም ወርም በፈረንሳይ ሊዮን ከተማ ተቋሙ በሚያዘጋጀው 47ኛው ዓለም አቀፍ የክኅሎት ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሦስት የሙያ መስኮች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ)፣ የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ እንዲሁም በማሽን ማምረት እንደሆነ ተነግሯል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በላቀ ደረጃ ውጤታማነቱን የሚያረጋግጥ የክኅሎት ልማት በተለይም ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ መሰረት ያደረገ ሪፎርም እየተዘጋጀ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ይህ መድረክ የእውቀት ልውውጥ፣ ዓለም ያለበትን የክህሎት ደረጃ እንዲሁም ደግሞ የኢንዱስትሪ ትስስርን ለመፍጠር ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የስራ እድልን በመፍጠር እውቅናን የሚሰጥ ነውም ብለዋል።
በሃይማኖት ኢያሱና ዳዊት ደያሳ