የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

By Melaku Gedif

August 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክር አቶ ፈንታሁን ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት ተሰርቷል፡፡

በዚህም መሰረት በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማጠናከር ባለፈ ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶች ላይ እድሳት እና ጥገና መከናወኑንም አስረድተዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመትም 11 ነጥበብ 5 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥና 232 ሺህ 900 በላይ የውጭ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን መጎብኘታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ከተለያዩ የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎቶች ከ36 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ ፋንታሁን፤ በተያዘው በጀት ዓመት የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ለማነቃቃት በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ