Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ስደተኞች ያሉበትን ቦታ እንዲንከባከቡ በማድረግ ትልቅ ተሞክሮ እያሳየች ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ብቻ ሳይሆን የሚኖሩበትን ቦታ እንዲንከባከቡ በማድረግ ረገድም ትልቅ ተሞክሮ እያሳየች መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በዚሁ ወቅት በችግኝ ተከላው የተሳተፉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦችን ያደነቁት አቶ ተመስገን÷ የዛሬው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ታኅሣስ 2023 በጀኔቫ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮንፈረንስ ላይ ቃል የገባችው የ100 ሚሊየን ችግኝ በአራት ዓመት የመትከል ግብ ማስጀመሪያ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጀኔቫ ቃል የገባችውን ከተቀመጠው ዓመት ባነሰ ጊዜ እንደምታጠናቅቅም አመላክተዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ ከተገኘው ውጤት የላቀ ለማስመዝገብ የታቀደውን በመተግበሩ ረገድ ሁሉም በኃላፊነት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዛሬውን የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ያስተባበረው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው÷ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቱን በመተግበር ሥራው የአረንጓዴ ዐሻራ ተሳትፎ አንዱ አካል ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም ተቋሙ በመላ ሀገሪቱ 5 ሚሊየን ችግኞችን ይተክላል ብለዋል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው

Exit mobile version