Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ24 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና የሕክምና ግብዓቶችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የሥራ ሃላፊዎች በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመገኘት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን አፅናንተዋል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ÷ ተቋማቸው ጉዳቱ ከተከሰተ ማግስት ጀምሮ የሕክምና ግብዓቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማትን በማስተባበር ለተጎዱ ወገኖች 5 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብና 15 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ግብዓት፣ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሁም ምግብ ነክ የሆኑ ድጋፎች ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የፌደራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ዘካርያ ÷ ለተጎዱ ወገኖች 2 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብና 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የአልባሳት፣ ንፅህና መጠበቂያና ምግብ ነክ ድጋፍ ማድጋቸውን ተናግረዋል።

የሐዋሳ፣ ቦሌ ለሚ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተባበር የዓይነት ድጋፍ መሠብሠቡን በመግለጽ በቀጣይ የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያደርጉም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ÷ ተቋማቱ ላበረከቱት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

Exit mobile version