Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) የሲቪል ሰርቫንት ደመወዝ ማሻሻያ በሚል የተሰራጨው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲቪል ሰርቫንት ደመወዝ ማሻሻያ በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የተሰራጨው መረጃ ሃሰተኛና ምንም ዓይነት የመነሻ መሰረት የሌለው መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

መኩሪያ ሃይሌ (ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትእንደገለጹት ÷የመንግስት ሰራተኞችን የደመወዝ ስኬል በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተናፈሱ የሚገኙ መረጃዎች ሃሰተኛ ናቸው፡፡

ማንኛውም ማሻሻያ ወይም የደመወዝ ስኬል ለውጥ ካለ ሕጋዊ ሰውነት ባላቸው እና በሚመለከታቸው አካላት ይፋ እንደሚደረግ  አስገንዝበዋል፡፡

ውሳኔዎቹ ሲኖሩም በዝርዝር ጥናቶች እና የበጀት አጸዳደቅ ሥርዓትን ተከትለው የሚካሄዱ መሆኑን ማጤን ጠቃሚ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ታማኝ እና ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት ሁልጊዜም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው  አካላት ማጣራት እና ማገናዘብ ከስህተት እንደሚታደግም አንስተዋል፡፡

በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎች አንዳንድ ጊዜ እውነታዎችን ሊያዛቡ ይችላሉ ያሉት ኮሚሽነሩ ÷ ይህም ግራ መጋባትን ከማስከተሉ ባለፈ ያልተፈለገ እንድምታ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ እየተናፈሱ የሚገኙት አሉባልታዎች እውነተኛ የመረጃ መሠረት እንደሌላቸው ገልጸው ÷ መሰል የሚሊየኖችን ሕይወት የሚነካ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ተገቢነት እንደሌለውም ጠቅሰዋል።

Exit mobile version