የሀገር ውስጥ ዜና

ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች

By Melaku Gedif

August 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ከዛምቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ጃኮብ ጃክ ምዊቡን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት አቶ ብናልፍ በኢትጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ልማት ከማረጋገጥ አንጻር በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራና በአይ ሲቲ ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሕገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመቀነስና በሕጋዊ መንገድ እንዲሔዱ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የዛምቢያ መንግስት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡

በዛምቢያ እና ኢትዮጵያ መካከል የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር መኖሩን ያነሱት ጃኮብ ጃክ ምዊቡን በበኩላቸው÷ ለአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣት ከፍተኛ ሚና ለነበራት ኢትዮጵያ ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በሰላምና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡

በተለይ ሀገራቸው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መተላፊያ መንገድ እንደመሆኗ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና እንግልት በዘላቂነት ለማስቀረት በትብብርና በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አቶ ብናልፍ÷የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ በማጠናከርና የጋራ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመዘርጋት የአፍሪካን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ብሎም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት ከምን ጊዜውም በላይ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡