Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዝቅተኛ የሥራ አፈፃፀም ያላቸው አመራሮች በአመራርነት ላይቀጥሉ ይችላሉ – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚሆን ሥራ ላይ ዝቅተኛ የሥራ አፈፃፀም የሚታይባቸው አመራሮች በአመራርነት ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አመላከቱ፡፡

የክልል ማዕከል፣ የአራቱም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ሐዋሳን ጨምሮ ከከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ2016 ዓ.ም ሥራ አፈፃፀም ግምገማ እንዲሁም የ2017 በጀት አመት እቅድ ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ይገኛል።

መድረኩ በ2016 በጀት አመት የተሠሩ ሥራዎች ላይ የታዩ ጥንካሬዎች እና ጉድለቶችን በመለየት ለቀጣይ የሥራ ዓመት በየደረጃው ያሉ አመራሮች በሁሉም ዘርፎች ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የሚዘጋጁበት መሆን እንዳለበትም ተመልክቷል።

ባለፈው በጀት ዓመት ምርጥ ተሞክሮ የሚሆኑ ሥራዎች እንዳሉ የተነሳ ሲሆን፥ በዚህም ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚሆን ሥራ የሠሩ እና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አመራሮች ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡

ሆኖም ዝቅተኛ የሥራ አፈፃፀም የሚታይባቸው በአመራርነት ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው፥ መድረኩ የመንግስትና ፓርቲ ሥራዎች በዕቅዱ መሠረት ምን ያህል እንደተፈፀሙ የሚፈተሽበት እና የታዩ ጉድለቶች የሚለዩበት መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በቀጣይ ዓመት በትኩረት ለመሥራት ዝግጅት የሚደረግበት መድረክ መሆኑን አመላክተዋል።

መድረኩ በቀጣይ እስከ ታችኛው መዋቅር እንደሚወርድ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version