አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ግምታዊ ዋጋቸው ከ58 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የመድሀኒት እና የህክምና መስጫ ቁሳቁሶችን አስረክቧል።
የመድሀኒት እና የህክምና መስጫ ቁሳቁሶቹ በክልሎቹ ለሚገኙ 32 የጤና ተቋማት የሚከፋፈል መሆኑ ተገልጿል።
ድጋፉ የህክምና ተቋማቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እና በሽታን ለመከላከል አስፈላጊውን ግብዓት እንዲኖራቸው እንደሚያግዝም ነው የተነገረው።
ማህበሩ ድጋፉን ያስረከበው ከእንግሊዝ መንግስት የውጪ የጋራ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር እያከናወነው ለሚገኘው ‘‘ኢትዮጵያ ቱ ረዚለንስ’’ ለተሰኘው የሁለት ዓመት ፕሮጀክት አፈፃፀምን እንዲደግፍ ነው ተብሏል።
ፕሮጀክቱ የጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋም እና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማገዝ እንደሚያስችል ተገልጿል።
በፍቅርተ ከበደ