አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ8 ቀናት ወደጠፈር የሄዱት ጠፈርተኞች እስከፈረንጆቹ 2025 ሊቆዩ እንደሚችሉ ተሰምቷል፡፡
ከሁለት ወራት በፊት አሜሪካውያን ጠፈርተኞች ወደዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የሙከራ ተልዕኮ ሲላኩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደምድር ይመለሳሉ ተብሎ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ነገሮች በተያዘላቸው እቅድ መሄድ ሣይችሉ ቀርተዋል፡፡
በዚህም እስካሁን ባሪ “ቡች” ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ ጠፈር ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፥ አሁንም በዚያው እንደሚቆዩ ነው የተገለጸው፡፡
የ61 ዓመቱ ዊልሞር እና የ58 ዓመቷ ዊሊያምስ የቦይንግ ስታርላይነር የጠፈር መንኮራኩር ሰዎችን ይዞ በመደበኛነት ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት እንዴት እንደሚሰራ ለማየት የተነደፈ ሙከራ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ሆኖም ያልተጠበቀ የቴክኒክ ችግር መፈጠሩም ነው የተገለጸው፡፡
ስለዚህ ወደ ጠፈር ጣቢያው በሰላም ቢደርሱም በስታርላይነር ወደ ምድር ለመመለስ ደህንነቱ የተጠበቀ ካልሆነ አማራጭ የመጓጓዣ ዘዴ ያስፈልጋቸዋል።
የናሳ ባለስልጣናት እስካሁን በዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰ ገልጸው፥ ሆኖም ግን ሌሎች አማራጮች እንዳሉን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እቅድ አዘጋጅተናል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
እየታሰበበት ያለው አንዱ አማራጭም ሁለቱን ጠፈርተኞች በመስከረም ወር ሊደረግ ከታቀደው ተልዕኮ ወደ ምድር እንዲመለሱ ማድረግ ሲሆን፥ ይህም በፈረንጆቹ 2025 የካቲት ወር ላይ መሆኑ ነው፡፡
ይህም የጠፈር ተመራማሪዎችን ከታቀደው የሥምንት ቀን ቆይታ ወደ ሥምንት ወራት የሚያራዝም እንደሆነም ነው የዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ያስታወቀው፡፡
በዚህም ተጨማሪ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ናሳ ለሁለቱ የጠፈር ተመራማሪዎች አልባሳትን ጨምሮ ምግቦችን እና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ስፔስ ኤክስ ሮኬት ተጠቅሟል ተብሏል።
የናሳ ባለስልጣናት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪደረግ ድረስ አንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል።
ባለፈው ወር በአጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠፈርተኞቹ ወደምድር እንደሚመለሱ እርግጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን አስታውሶ የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡