Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሐረሪ ክልል መስተዳድር ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ካቢኔው በዋናነት የመሠረተ ልማት ሥራዎች ቅንጅት፣ ጥበቃና የአሠራር ሥርዓትን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ በስፋት ተወያይቶ አጽድቋል።

የመሠረተ ልማት ሥራዎች ቅንጅት፣ ጥበቃና የአሠራር ሥርዓትን ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና የተቀናጀ የመሰረተ ልማት እና ግንባታ ሥርዓት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሰፍን የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል።

በተለይም ደንቡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እርስ በርስ የተናበቡ፣ ተደራራቢ ወጪዎችን በመቀነስ ዘላቂ ልማትን የሚያስገኙና የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ተብሏል።

የመሠረተ ልማት ሥራዎች ጉዳት ሊያደርሱባቸው የሚችሉ ስጋቶችን ለመቀነስ እንዲቻል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራና የተናጥል አቅምና ሃላፊነት ለማሳየት የሚያስችል ግልጽ የአሠራር ሥርዓትን ለማስቀመጥ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

ካቢኔው በደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ከዛሬ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ ካቢኔው ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡

Exit mobile version