Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሐምሌ ወር የሰለጠነ የሰው ሃይል ወደ አውሮፓ ሀገራት መላክ ተጀምሯል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐምሌ ወር የሰለጠነ የሰው ሃይል ወደ አውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ፤ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዕቅድ አፈፃፀም ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ ልምዶችን በመውሰድ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን ሚና በአግባቡ በመለየትና በማቀድ ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ሃይል ቀደም ሲል ከነበረው የመካከለኛ ምስራቅ መዳረሻ በተጨማሪ ወደ አውሮፓ ሀገራት መላክ መጀመሩ በወሩ ከተመዘገቡ ውጤታማ ስራዎች ውስጥ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል ወ/ሮ ሙፈሪሃት።

አገልግሎት አሰጣጡም ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሁም አጠቃላይ ስምሪቱ የዜጎችን መብትና ደህንነት ያስጠበቀ እንዲሆን በማድረግ በሐምሌ ወር 26 ሺህ 195 ዜጎችን አሰልጥኖ ለሥራ ማሰማራት መቻሉም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርና ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያው የሚያመጣውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም የማሰልጠኛ ተቋሞችን በአግባቡ አደራጅቶ ጥራት ያለው ስልጠና እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡

አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ሥራውን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ በዘርፉ እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ እንዲሁም ሚናን እየተወጡ ለሚገኙ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡

Exit mobile version