አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሰው ኃይል ልማት በመጀመር የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለማልማት የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፍ የቻይና የኒውክሌር ኃይል ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሊጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በቤጂንግ የሚገኘውን የኒውክሌር ምርመር እና ሪአክተር ማዕከል እንዲሁም የቻይና የኒውክሌር ኃይል ባለስልጣንን ጎብኝተዋል፡፡
ከጉብኝታቸው በኋላም ከባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሊዩ ጂንግ ጋር ከዚህ በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል የተደረጉ ስምምነቶች መሰረት በተለይም ከሰው ሀብት ልማት አኳያ በትብብር መሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ቻይና የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ጥቅም በማዋል ረገድ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ መድረስ እንደምትፈልግ ያስረዱት ሚኒስትሩ÷ እስከ አሁንም በዘርፉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ለማሰልጠን እያደረገች ላለው ድጋፍ በማመስገን ትብብሯ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በኒውክሌር ትምህርት እና ምርምር ዘርፍ ከቻይና ዩኒቨርሲቲዎች እና ተቋማት ጋር በትብብር የሚሠሩበትን ዐውድ ለማስፋት በሚቻልበት አግባብ ላይም መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኃይል ኤጀንሲ (አይ ኤ ኢ ኤ) ጋር በቅርበት እየሠራች መሆኗን በመግለጽ ከተቋሙ ጋር በኢትዮጵያ የአፍሪካ የስልጠና ማዕከል ለመገንባት ኢትዮጵያ ለኤጀንሲው ያቀረበችውን ጥያቄ ባለስልጣኑ እንዲደገፍ ጠይቀዋል።
ሊዩ ጂንግ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከሰው ኃይል ልማት በመጀመር የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለማልማት የጀመረችውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል፡፡
በመስከረም ወር በፎካክ በሚደረገው ስብሰባ በአፍሪካ ኅብረት፣ በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም እና ቻይና መካከል በአፍሪካ የስልጠና ተቋም ለማቋቋም የሦስትዮሽ ስምምነት እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ለአፍሪካ ኅብረት እና ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው÷ ይህ የባለብዙ ወገን ስምምነት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከልም በጋራ ሊሠሯቸው በሚፈልጓቸው ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት መደረግ እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።