የሀገር ውስጥ ዜና

ግለሰብን በማስፈራራትና በመደብደብ ንብረት ወስደዋል ተብለው የተጠረጠሩ የፖሊስ አባላት ፍ/ቤት ቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

August 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሌሊት ለወንጀል መከላከል ሥራ በተሰማሩበት ቦታ ግለሰብን አግተው በሽጉጥ አስፈራርተው ንብረት ወስደዋል ተብለው ስልጣንን ያለ አግባብ መገልገል ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት የፖሊስ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት÷ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የሐርቡ ፖሊስ ጣቢያ አባል የሆኑት ረዳት ሳጅን ሬድዋን ሁሴን እና ኮንስታብል ሳሙኤል ድጉማ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ያቀረበው የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መርማሪ÷ ተጠርጣሪዎቹ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሌሊት በወንጀል መከላከል ሥራ ላይ ተመድበው ሲሠሩ መንገድ ላይ ያገኙዋቸውን አንድ የግል ተበዳይ መታወቂያ አምጡ በማለት ፖሊስ ጣቢያ እንደወሚወስዷቸው ገልጸው ግለሰቡ በኪሳቸው የያዙትን ሁለት ዘመናዊ ሞባይሎች በሽጉጥ አስፈራርተው በመደብደብ እንደወሰዱባቸው ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ከግለሰቡ የተወሰዱትን ስልኮች 2ኛ ተጠርጣሪ በመኖሪያ ቤቱ በሚተኛበት ፍራሽ ውስጥ ደብቆ መገኘቱን ጠቅሶ በተጠረጠሩበት ስልጣንን ያለ አግባብ መገልገል ወንጀል ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ገልጸው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው የጠቀየቁ ሲሆን÷ መርማሪ ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ ምርመራው ሳይጠናቀቅ በዋስ ቢወጡ የግል ተበዳዩን ሊያስፈራሩ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል።

ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱም ከቀሪ የምርመራ ሥራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የሰባት ቀን የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ