የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 351 የንግድ ተቋማት ታሸጉ

By Melaku Gedif

August 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርት በሸሸጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ እንዳሉት÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ተከትሎ በክልሉ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርት በሸሸጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል፡፡

ቢሮው ሰሞኑን ባደረገው ክትትልም 351 የንግድ ቤቶች መታሸጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

ከታሸጉት የንግድ ቤቶች መካከል 12ቱ የንግድ ዕቃ ማከማቻ መጋዝናቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሲሆን÷ ባለቤቶቹም በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ሌሎች የንግድ ተቋማት የዋጋ ዝርዝር ባለመለጠፍ፣ ያልተገባ ዋጋ በመጨመር እና ምርት በመደበቃቸው እንዲታሸጉ መደረጉንም ሃላፊው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

እንደፈጸሙት ተግባር በታሸጉ የንግድ ተቋማት ላይ የንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመው÷ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።