ስፓርት

‘አሰልጣኟ አይደለህም፣ አናውቅህም’ ተብየ ኦሊምፒኩን እንዳልከታተል ተደርጌያለሁ – የአትሌት ጽጌ ዱጉማ አሰልጣኝ

By Melaku Gedif

August 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘አሰልጣኟ አይደለህም፣ አናውቅህም’ ተብየ ኦሊምፒኩን እንዳልከታተል ተደርጌያለሁ ሲል የአትሌት ጽጌ ዱጉማ አሰልጣኝ ዓለሙ ዋቅጅራ ተናገረ፡፡

አሰልኙ የፓሪስ ኦሊምፒክ መለያ ባጅ መከልከሉን ተክትሎ በኢትይጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ላይ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ዓለሙ ዋቅጅራ÷ ኦሊምፒኩን ለመከታተል እና የ800 ሜትር አትሌቷን በአሰልጣኝነት ለማገዝ ከኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ልዑክ ጋር ወደ ፓሪስ ማቅናቱን አንስቷል፡፡

ይሁን እንጂ በፓሪስ ቆይቶ ሀላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለውን መለያ ባጅ መከልከሉን ገልጿል፡፡

በመሆኑም ለማረፊያ፣ ለመመገብ፣ ስታዲየም ለመግባት እና የአሰልጣኝነት ስራውን ለማከናወን የሚያግዘውን የመለያ ባጅ ባለማግኘቱ ከፓሪስ ለመመለስ ተገዷል።

ከብዙ ክርክር በኋላ የመለያ ባጅ ማግኘቱን ገልጾ÷ በሁለተኛው ቀን መለያ ባጁ መቀየሩን እና የተቀየረው መለያ ባጅ ደግሞ ሆቴል መመገብ፣ ስታዲየም መግባት እና መንቀሳቀስ የማያስችል እንደነበር ገልጿል፡፡

በመጨረሻም ለአትሌት ጽጌ ዱጉማ አሰልጣኟ አይደለህም፣ አናውቅህም ተብየ በሀይል የሆቴል ክፍሌን እንድለቅ እና ወደ ሀገሬ እንደመለስ ተደርጌያለሁ ብሏል፡፡

ለወራት በስልጠና ዝግጅት ሲያግዛት የነበረችው ጽጌ ዱጉማ የብር ሜዳሊያ በማምጣቷ መደሰቱን የገለፀው አሰልጣኙ፤ ነገር ግን ውድ ልጁን ስታዲያም ተገኝቶ የአሰልጣኝነት ድጋፉን ባለመስጠቱ ማዘኑን በቁጭት ገልጿል፡፡

የተደረገበት ክልከላ ተገቢ አለመሆኑን የገለፀው አሰልጣኙ÷ አትሌቲክሱን የሚመሩ ሰዎች የሚፈፅሙት ተገቢነት የሌለው ተግባር እንዲቆም ጠይቋል፡፡

 

 

 

በሚኪያስ አየለ እና ወርቅነህ ጋሻው